Tuesday, July 14, 2015

ርዕዮት ዓለሙ፤ ኤዶም ካሣዬና ማኅሌት ፋንታሁን ተፈቱ



"መልካም ኢትዮጵያን፣ ፍትሕ የሠፈነባት ኢትዮጵያን፣ ዴሞክራሲ ያለባት ኢትዮጵያን እስከማይ ትግሌ ይቀጥላል" - ርዕዮት ዓለሙ
ርዕዮት ዓለሙ
ርዕዮት ዓለሙ
ሰሎሞን አባተመለስካቸው አምሃሰሎሞን ክፍሌ
የአዲስ ፕሬስ ጋዜጣ አዘጋጅ፣ በፍትሕ ጋዜጣና ለአጭር ጊዜ ወጥቶ በነበረው ቼንጅ መፅሔት አምደኛ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሪቪው ዌብሣይት ሪፖርተር ሆና እየሠራች ሳለች ታሥራ የነበረችው ርዕዮት ዓለሙ ዛሬ ረፋድ ላይ ተለቀቀች፡፡
ርዕዮት የተለቀቀችው ተፈርዶባት ከነበረው የአምስት ዓመት እሥራት 4 ዓመት ከ17 ቀኑን ጨርሳ ነው፡፡
ርዕዮት የተለቀቀችበት ደብዳቤ በአመክሮ እንደተለቀቀች ቢናገርም በአመክሮ መለቀቅ የነበረባት ባለፈው ጥቅምት እንደነበረ ጠበቃዋና አባቷ አቶ ዓለሙ ጎቤቦና ርዕዮት እራሷም ገልፀዋል፡፡
ርዕዮት ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር፣ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሣተፍ እና በሕገወጥ የገንዘብ ሽግግር ወንጀሎች ተከስሳ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የ14 ዓመት እሥራትና የ33 ሺህ ብር መቀጫ ተፈርዶባት የነበረ ቢሆንም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ መሣተፍ ከሚለው በስተቀር ሌሎቹን ክሦች ውድቅ አድርጎ እሥራቱን ወደ አምስት ዓመታት ዝቅ እንዲል፤ የገንዘብ ቅጣቱም እንዲሠረዝ መወሰኑ ይታወሣል፡፡ 
ርዕዮት ዓለሙ ዛሬ ለቪኦኤ በሰጠችው ቃል መልካም ኢትዮጵያን፣ ፍትሕ የሠፈነባት ኢትዮጵያን፣ ዴሞክራሲ ያለባት ኢትዮጵያን እስከማይ ትግሌ ይቀጥላል ብላለች ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ትናንት ድንገት ከተለቀቁት የዞን ዘጠኝ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ጋር ይለቀቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበሩት ጋዜጠኛ ኤዶም ካሣዬ እንዲሁም መምህርና ብሎገር ማኅሌት ፋንታሁን ዛሬ መለቀቃቸው ታውቋል፡፡
በስሙ የምኅፃር አጠራር ሲፒጄ እየተባለ የሚታወቀው ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት በኢትዮጵያ ሦስት ጋዜጠኞችና ሁለት የዞን - ዘጠኝ አምደኞች ወይም ብሎገሮች ከእሥር መለቀቃቸው ያስደሰተው መሆኑን ገልጿል።
በጋዜጠኞቹ ላይ የቀረቡ፥ ሕዝብን ለአመፅ የማነሳሳትና የሽብር ፈጠራ ክሶችም መሠረዛቸው ተዘግቧል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ደግሞ እስክንድር ነጋና ውብሸት ታየን ጨምሮ ሌሎቹም እሥረኞች እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡
ለተሟሉ ዘገባዎች የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

No comments:

Post a Comment